“ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኤአይ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ትልቅ አቅም አላት፡፡” የዓለም ጤና ድርጅት (WHO)
· Visiting
WHO and EAII Explore AI Collaboration to Expand Accessible and Innovative Healthcare Services
ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የመጡ ልዑካን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ጎብኝተው፣ በጤናው ዘርፍ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ አብሮ መሥራት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ከኢንስቲትዩቱ አመራሮች ጋር ተወያዩ።
የልዑካን ቡድኑ አባላት ኢትዮጵያ በኤአይ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ አቅም እንዳላት ተናግረዋል። የኢንስቲትዩቱ ምክትል
ዋና ዳይሬክተር ታዬ ግርማ (ዶ/ር) በበኩላቸው የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ የተዘጋጁ የኤአይ መፍትሔዎችን አስተዋውቀዋል። ሁሉም ዜጋ ከቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆን ሰፊ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።
በውይይቱ ወቅት ኤአይ የጤናውን ዘርፍ እንዴት ሊለውጠው እንደሚችል፣ በአንደኛ ደረጃ የጤና ተቋማት ውስጥ እንዴት ሥራ ላይ ሊውል እንደሚችል እንዲሁም የሕክምና ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ የሚረዱ መንገዶች ላይ ሃሳብ ተለዋውጠዋል።
ኢንስቲትዩቱ በተፈጥሮ ቋንቋ ቅንብር (NLP) ያከናወናቸው ሥራዎች አስደናቂ መሆናቸውን በመግለጽም፣ የማሽን ቋንቋ እና የንግግር ማወቂያ ቴክኖሎጂዎች ለጤናው ዘርፍ ሰፊ ጠቀሜታ እንዳላቸው አስምረውበታል።
የልዑካን ቡድኑ አባላት እንደ ኤአይ ያሉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በአህጉሪቱ ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ጠቁመው፤ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በጋራ ለመሥራትና አጋርነትን ለማጠናከር ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው አረጋግጠዋል።
Source: Ethiopian Artificial Intelligence Institute