በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የለማ የተቀናጀ የሚዲያ ሬጉላቶሪ እና አስተዳደር ሥርዓት ተመረቀ
· Other
EAII Launches Digital Media Governance System to Enhance Transparency, Combat Misinformation, and Boost National Productivity.
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ያለማው የተቀናጀ የሚዲያ ሬጉላቶሪ እና አስተዳደር ዲጂታል ሥርዓት በዛሬው ዕለት በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተመርቋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ይህ ዘመኑን የዋጀ የዲጂታል ሥርዓት በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የሚዲያ ተቋማትን በዘመናዊ መንገድ ለመምራት፣ ለመቆጣጠር እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ሥርዓቱ በዋናነት የሚዲያ ተቋማትንና ባለሙያዎችን ምዝገባ በዲጂታል መልኩ ለማከናወን ያስችላል፡፡
ፍቃድ ያደሱና ያላደሱ የሚዲያ ተቋማትንም በቀላሉ ለመለየት ይረዳል። በተጨማሪም ማህበረሰቡ በሚዲያዎች ላይ የሚስተዋሉ የሀሰት ዜናዎችን፣ የጥላቻ ንግግሮችን እና ሕገ-ወጥ ማስታወቂያዎችን በድረ-ገጽ ወይም በሞባይል መተግበሪያ አማካኝነት በቀጥታ ጥቆማ እንዲሰጥ ዕድል ፈጥሯል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው ሥርዓቱ በከፍተኛ ጥራትና በአጭር ጊዜ መጠናቀቁን አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሐይማኖት ዘለቀ ፥ ኢንስቲትዩቱ ያለማው ይህ ሥርዓት የሚዲያ ተቋማትን ምዝገባና መረጃ ከማደራጀት ባለፈ የሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ስርጭትን ለመቆጣጠር የሚያስችል በመሆኑ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ መገናኛ ብዙኃንን በሥነ-ምግባር አከባበራቸው ላይ በመመስረት በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ደረጃዎች በመመደብ ግልጽ የሆነ የክትትል ስርዓት ይዘረጋል። በአጠቃላይ ሥርዓቱ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን በመቀነስ ረገድ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እና በዘርፉ ተዓማኒነት ያለው የመረጃ ፍሰት እንዲሰፍን በማድረግ ለሀገራዊ ግንባታ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
Source: Ethiopian Artificial Intelligence Institute