የኤ.አይ ቴክኖሎጂን ለማልማትና የጥናትና ምርምር ስራዎችን በጋራ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መካከል ተደረገ።
· MOU
EAII and the University of Gondar sign partnership to strengthen AI research, capacity building, and collaboration.
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተደረገውን ስምምነት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ደሳለኝ እና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) ፈርመዋል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ደሳለኝ የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግና ለመጠቀም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና የላቀ መሆኑን ተናግረዋል። ከዩኒቨርሲቲው ጋር የተደረገው ስምምነትም የዚሁ አካል መሆኑን የጠቀሱት ም/ዋና ዳይሬክተሩ ፥ ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እያደረገ ላለው ጥረት ተጨማሪ እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው በአጭር ጊዜ ተቋቁሞ ከእድሜው በላይ የሆኑ ተግባራትን መከወን ከቻለ ተቋም ጋር መስራታችን ሰፊ ዕድሎች አሉት ብለዋል። ስምምነቱ በወሳኝ ጊዜ እና ምዕራፍ መደረጉን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ ፥ ዩኒቨርሲቲው በኤ.አይ መስክ የጀመራቸውን ስራዎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረገው ስምምነት በክልሉ በተለዩ መስኮች ላይ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በጋራ ለማከናወን፣ ችግር ፈቺ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ፣ የቴክኒክ ድጋፎችን ለማድረግ እና መረጃ ለመለዋወጥ የሚያስችል ነው።
ከስምምነቱ በተጓዳኝ በጎንደር ብሔራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኮንፍረንስ ለማዘጋጀት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ተደርጓል።
Source: Ethiopian Artificial Intelligence Institute