የአካባቢ ብክለትን በቀላሉ ሪፖርት ለማድረግ የሚያስችል ዲጂታል ሥርዓት በይፋ ተመረቀ፡፡
· Other
EAII Launches Digital Pollution Reporting System to Strengthen Environmental Protection, Public Participation, and National Productivity
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ያለማው የአካባቢ ብክለት ሪፖርት ማድረጊያ ዲጂታል ሥርዓት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል፡፡
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ኢንስቲትዩቱ ከምስረታው ጀምሮ በተለያዩ ዘርፎች ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የኤ.አይ ውጤቶችን ሲያለማ መቆየቱን በመርሃግብሩ አስታውሰዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ከአካባቢ ጥበቃ ረገድ የራሱን አሻራ ለማኖር ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸው፤ በተለይም 32ኛውን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ (COP32) ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ለምትገኘው ኢትዮጵያ ይህን መሰል ሥርዓቶች መኖራቸው ወሳኝ ነዉ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ( ዶ/ር) በምርቃት መርሃግብሩ ወቅት ባስተላልፉት መልዕክት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአካባቢ ጥበቃ ላይ ቸልተኝነት እንዳይኖር ዜጎችን ለማሳተፍ ሲስተሙ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጽዱ ኢትዮጵያን ለማረጋገጥ ባለስልጣኑ እየሰራ የሚገኘው ስራ እውን እንዲሆን ኢንስቲትዩቱ ላሳየው ትብብርም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የመርሃግብሩ የክብር እንግዳ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲዔታ በረከት ፍሰሃጺዮን በበኩላቸዉ ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ የያዘችው እቅድ ውጤታማ እንዲሆን ኢንስቲትዩቱ እንዲሁም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሚናቸውን በአግባቡ እየተወጡ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በይፋ የተመረቀው ዲጂታል ሥርዓት ዜጎች በአካባቢያቸው የሚደርስን ብክለት በሞባይል እና በዌብፖርታል አማካኝነት እንዲጠቁሙ የሚያስችል ነው፡፡
Source: Ethiopian Artificial Intelligence Institute