የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስራ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
· MOU
“Partnership to Enhance Judicial Efficiency Through Advanced Speech-to-Text Technology”
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኤ.አይ የታገዘ ንግግርን ወደ ጽሁፍ መቀየሪያ ሥርዓት (AI Based Transcription system) ለማልማት የውል ስምምነት አድርገዋል፡፡ ስምምነቱ በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የሚደረጉት የፍርድ ቤት የቃል ክርክሮችን ወደ ጽሁፍ ለመቀየር የሚያስችል ሥርዓት ለማልማት የተደረገ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ስምምነቱን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ኢንስቲትዩቱ የትኩረት መስኩ አድርጎ ከሚሰራባቸው መስኮች አንዱ የተፈጥሮ ቋንቋ ቅንብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም የህዝቡን ችግር የኤ.አይ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ለመፍታት ኢንስቲትዩቱ ቁርጠኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ለዚህም ስምምነቱ አንድ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የተከበሩ አቶ ገዛሊ አባሲመል የቃል ክርክሮችን በጽሁፍ ግልባጭ ለማድረስ የሚወስደው ጊዜ የፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ትልቅ ችግር ሆኖ መቆየቱን በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡ በዚህም ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናን ለማረጋገጥ ከኢንስቲትዩቱ ጋር የተደረገው ስምምነት ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ልዑካን ከስምምነቱ ጎን ለጎን አዲሱ የኢንስቲትዩቱን ዋና መስሪያ ቤት ጎብኝተዋል፡፡
Source: Ethiopian Artificial Intelligence Institute