“ኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽንን እና ቴክኖሎጂን በሁሉም ዘርፎች ለመጠቀም ምን ያህል ትልቅ ራዕይ እንዳላት እናውቃለን” ሲንካ አንቲላ በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር
· Visiting
The Finnish Ambassador explored EAII’s AI innovations and discussed expanding Ethiopia–Finland cooperation in digital technology.
በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ሲንካ አንቲላ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን የስራ እንቅስቃሴ ለማየት እና የሁለቱን ሀገራት የቴክኖሎጂ ትብብር ለማጠናከር የሚያስችል የስራ ጉብኝት አድርገዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸ (ዶ/ር) ለአምባሳደሯ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፤ በጉብኝቱ ወቅት ኢንስቲትዩቱ በሮቦቲክስ፣ በጤና እና በሌሎች ቁልፍ የቴክኖሎጂ ዘርፎች እየተገበራቸው ስላሉት ፕሮጀክቶች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በተለይም የ"ሞሰብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና የስታርታፕ ማዕከሉ ለሀገር በቀል ፈጠራዎች እየሰጠ ያለው ድጋፍ፣ ለኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ያለውን ፋይዳ አስረድተዋል።
አምባሳደር ሲንካ አንቲላ በኢንስቲትዩቱ የታዘቡት የቴክኖሎጂ አቅም እና የፈጠራ ስራዎች በእጅጉ አስደምሟቸዋል። አምባሳደሯ ከኢትዮጵያ ጋር የቆየውን የትምህርት እና የልማት ትብብር ወደ ዲጂታል ዘርፉ ማሸጋገር ተገቢ መሆኑን አንስተዋል። አያይዘውም ከ135 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ላላት ኢትዮጵያ፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
ፊንላንድ በየዓመቱ በህዳር ወር ከዓለም ዙሪያ ኢንቨስተሮችና ስራ ፈጣሪዎች የሚገናኙበትን 'Slush' የተባለ ትልቅ ዝግጅት እንደምታዘጋጅ በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያም በጤና፣ በግብርና እና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ያሉ ድንቅ ፈጠራዎችን ሊደግፉ የሚችሉ የግል ኢንቨስተሮችን ለመሳብ እንደ 'Slush' ዓይነት ዝግጅቶች እንደሚያስፈልጓት ተናግረዋል።
Source: Ethiopian Artificial Intelligence Institute