የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የታዳጊዎች የክረምት ስልጠና የምርቃት መርሓ ግብር ተካሄደ።
· Education
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የታዳጊዎች የክረምት ስልጠና የምርቃት መርሓ ግብር ተካሄደ።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሚያዘጋጀው ዓመታዊው የኤ.አይ የታዳጊዎች የክረምት ስልጠና የምርቃት መርሓ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በክብር እንግድነት በተገኙበት በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርሓ ግብሩ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት መንግሥት በትኩረት ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል የሰው ኃይል አቅም ግንባታ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ስልጠናም ይህንን ጥረት ዕውን ለማድረግ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
ታዳጊዎች ይህን መሰል ስልጠና ማግኘታቸው ለነገዋ ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ መሆኑንም አክለዋል። ስልጠናው ሀገራችንን በማይቀረው የኤ.አይ አብዮት ውስጥ ተወዳዳሪ ለማድረግ አስቻይ ነው ብለዋል። የዛሬው ተመራቂዎች በስልጠናው ያገኙትን እውቀት እና ክህሎት ወደ ተግባር እንዲለውጡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የዘመኑ ግንባር ቀደም ቴክኖሎጂ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱም ታዳጊዎችን በዘርፉ በማሰልጠን ዘንድሮ አራተኛ ዙር ላይ መድረሱን አመላክተዋል። ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ሰልጣኞቹ በዚህ ስልጠና ያሳዩት ትጋት፣ ሥነ-ምግባር እና የፈጠራ አቅም ለኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
ለአራተኛ ዙር በተካሄደው የሰመር ካምፕ ስልጠና ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ 300 ታዳጊዎች ተሳትፈዋል። ተማሪዎቹም በኮምፒዩተር ቪዥን፣ ኤ.አይ ቤዚክስ፣ ፕሮግራሚንግ፣ ሮቦቲክስ፣ ማሽን ለርኒንግ እና በተፈጥሮ ቋንቋ ቅንብር መስኮች ዙሪያ ለሁለት ወራት ሰልጥነዋል።
Source: Ethiopian Artificial Intelligence Institute