የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የጤናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ ለማዘመን ከጤና ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ::
· MOU
The agreement will accelerate AI-powered healthcare innovation and support the implementation of the Digital Ethiopia 2030 strategy.
የሥምምነቱ ዓላማ በቴክኖሎጂ የታገዘ ፍትሃዊ፣ ጠንካራ እና ሰውን ማዕከል ያደረገ የጤና ሥርዓትን መገንባት ነው። የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቴክኖሎጂ ዘርፍ የሰነቁትን አርቆ አሳቢ ራእይ እና የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ራዕይን በተግባር ለማሳካት የተደረገ ትልቅ እርምጃም ነው።
የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ስምምነቱ በሀገራችን የሕክምና ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ ኤ.አይን እና ዲጂታል ጤናን በግንባር ቀደምትነት ለመምራት ለያዘችው አቅጣጫ እና ስኬት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እየሰጡት ላለው አመራር እና ድጋፍ አመስግነዋል። አክለውም መረጃዎችንና ዕውቀቶችን በመጋራት የሀገራችን የጤና ስርዓት እናሻሽላለን ብለዋል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ‘ኤ.አይ ለሁሉም’ በሚል እየሰራ መሆኑን አድንቀው ስምምነቱ የኤ.አይ ቴክኖሎጂ በተለይም በገጠር ለሚገኙ እናቶችና ሕፃናት ፍትሃዊ የጤና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም በውጭ ሀገር የሚገኙ የዲያስፖራ ባለሙያዎችን ከሀገራቸው ጋር ለማገናኘት ትልቅ አጋዥ መሣሪያ እንደሚሆን ገልጸዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የታደሙት የዓለም ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የጤና፣ ሥርዓተ-ምግብና የሕዝብ ቁጥር (HNP) ፕራክቲስ ማናጀር ዶ/ር ኤርነስት ማሳያ በበኩላቸው የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ተሞክሮ በመላው አፍሪካ ላሉ አገራት ድጋፍ መስጠት የሚችሉ የልህቀት ማዕከላትን ለመገንባት እና አህጉራዊ ራእይን ለማሳካት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ከመግባቢያ ስምምነቱ በተጨማሪ የጤና አገልግሎትን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ እንዴት ማሻሻል ይቻላል በሚለው ሀሳብ ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡
Source: Ethiopian Artificial Intelligence Institute