የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በጋራ መስራት በሚያስችላቸዉ ጉዳዮች ዙሪያ ዉይይት አካሄዱ።
· Visiting
EAII and the Disaster Risk Management Commission discuss AI-driven collaboration to strengthen disaster preparedness.
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) የኮሚሽኑን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተቀብለዉ አነጋግረዋል።
በዉይይቱ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የዲጂታላይዜሽን ሰነድ ቀርቦ ዉይይት ተደርጎበታል። በዚህም ኮሚሽኑ አሰራሩን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ በሚያከናዉነዉ ተግባር ዉስጥ ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሚጠበቁ ጉዳዮች በዝርዝር ተመላክተዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታዬ ግርማ (ዶ/ር) ኢንስቲትዩቱ ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። በውይይቱ የቀረቡት ጉዳዮች በቀጣይ በሚደረጉ ግንኙነቶች ዳብረው ወደ ስራ እንዲገቡ እንደሚደረግም አስታዉቀዋል።
የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራዉ ተክለማርያም (ዶ/ር) በበኩላቸዉ ኮሚሽኑ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በማዘመን ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ጋር የማጣጣም ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል። በዚህም የግብዓቶችን ክምችት፣ ዝዉዉር እንዲሁም ለኮሚሽኑ የሚቀርቡ ድጋፎችን መከታተል የሚያስችል ሥርዓት ለማልማት ከኢንስቲትዩቱ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
ሥርዓቶቹ መልማታቸዉ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም አደጋን የመቋቋም ብቃቷን በቴክኖሎጂ ለማዳበር የሚያስችሉ መሆናቸዉ በዉይይቱ ተመላክቷል።
Source: Ethiopian Artificial Intelligence Institute