የኤ.አይ ዩኒፖድ አፍሪካን ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወደ ንቁ ተሳታፊነት ለመቀየር የሚያስችል መሰረት መሆኑ ተገለጸ።
· Education
AI UniPod Innovation Center inaugurated to position Ethiopia as a creator in Africa’s growing digital economy.
ይህ የተገለፀው የኤ.አይ ዩኒፖድ (Al UniPod) የፈጠራ ማዕከል በይፋ በተመረቀበት ወቅት ነው፡፡
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ኤ.አይ ዩኒፖድ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መስክ ለሚሰሩ አካላት ዘር የመዝራት ሂደት ነው ብለዋል። ኤ.አይ ዩኒፖድ የቴክኖሎጂው ተመራማሪዎችን ከገበያው ጋር የማስተሳሰሪያ እድል መሆኑንም ገልጸዋል። ይህም ኢትዮጵያን በአፍሪካ የኤ.አይ ሥነ-ምህዳር አህጉራዊ የስበት ማዕከል ያደርጋታል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸዉ የማዕከሉ መከፍት ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂዉ ዘርፍ የሰጠችዉን ትኩረት ያመላክታል ብለዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማዕከሉን በሰዉ ኃይል እንደሚደግፍ እንዲሁም በአካዳሚክ ጉዳዮች አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን እንደሚያቀርብ ገልጸዋል። ይህም ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 መሳካት አጋዥ እንደሚሆን በንግግራቸዉ አንስተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ረዳት ዋና ፀሐፊ እና የዩ.ኤን.ዲ.ፒ የአፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር አሁና ኢዚያኮንዋ በበኩላቸዉ ኤ.አይ ለዘላቂ የእድገት ግቦች መሳካት ተጨማሪ አቅም እየሆነ ነዉ ብለዋል። ኤ.አይ ዩኒፖድ በቴክኖሎጂዉ መስክ ለተሰማሩ ሁሉም አካላት የተዘጋጀ የአፍሪካን እምቅ አቅም ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል ማዕከል መሆኑን አስታዉቀዋል።
በአፍሪካ የስራ ፈጠራና ስታርታፕን በሚደግፈው ቲምቡክቱ ኢኒሼቲቭ መሰረት የተቋቋመዉ ኤ.አይ ዩኒፖድ የኢትዮጵያን የኤ.አይ ቴክኖሎጂ ሥነ-ምህዳር ለማጎልበት ወደስራ ገብቷል።
ማዕከሉ ዕውን የሆነው በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በዩ.ኤን.ዲ.ፒ ትብብር ነው፡፡
Source: Ethiopian Artificial Intelligence Institute