የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለጉምሩክ ኮሚሽን ያለማቸው የጉምሩክ የስራ ሂደቶችን የሚያዘምኑ ዲጅታል ሥርዓቶች በይፋ ተመረቁ፡፡
· AI Solutions
Prime Minister Abiy Ahmed Inaugurates Advanced Digital Systems to Combat Corruption, Enhance Customs Efficiency, and Accelerate Ethiopia’s Digital Transformation.
በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርቃት መርሓ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ዲጂታል ሥርዓቶቹ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ሙስና እና ሌብነትን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ሥርዓቶችን የማጠናከር ስራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል።
በዛሬው ዕለት ለምርቃት የበቁት ዲጂታል ሥርዓቶች ጭነቶችን ከመነሻ እስከ መዳረሻ ለመቆጣጠር የሚያስችል የኤሌክትሮኒክ ካርጎ መከታተያ ሥርዓት እና የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስማርት የጉምሩክ የድንበር ቁጥጥርና አስተዳደር ሥርዓት ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም በአውሮፕላን ለሚገቡ መንገደኞች የጉምሩክ ፍተሻን የሚያቀላጥፍ የመንገደኞች ስጋት አስተዳደር ሥርዓት እና ተገልጋዮች የኮሚሽኑን አገልግሎቶች በ4 ቋንቋዎች በቻት ቦት አማካኝነት የሚያገኙበት የጉምሩክ መጋዘንና ወኪሎች የፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓት ናቸው፡፡
ሥርዓቶቹ ዲጅታል ኢትዮጵያን ዕውን በማድረግ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር እና የተሳለጠ የንግድ ሥርዓትን ለማስቻል አቅም ይፈጥራሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር የሸቀጦችን ደህንነት አስጠብቆ በፍጥነት እና በአነስተኛ ወጪ ለማጓጓዝ፣ በዓለማቀፍ ደረጃ የሀገራችንን የሎጂስቲክስ ደረጃ ለማሻሻል እና በጉምሩክ ጣቢያዎች ለሚፈጠሩ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችሉ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ላበለፀጋቸው ሲስተሞች የእውቅና ሽልማት አበርክተዋል።
ሥርዓቶቹን ከማስመረቅ ጎን ለጎን 7ኛው የታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
Source: Ethiopian Artificial Intelligence Institute