የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከከፍተኛ የትምህርትና የጤና ተቋማት ጋር ስትራቴጂካዊ ጥምረት መሰረተ
· MOU
EAII Signs New Partnerships to Expand AI Education, Research, Healthcare Innovation, and National Productivity in Ethiopia.
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሀገሪቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በቴክኖሎጂ ለመፍታትና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ያለመ የመግባቢያ ስምምነት ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ፣ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ እና ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ጋር ተፈራረመ።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ የሀገርን ችግሮች በኤ.አይ (AI) ቴክኖሎጂ ለመቅረፍ ከትምህርት ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ ይቀጥላል። ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፣ ስምምነቱ የኢትዮጵያን የነገ ተተኪ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን ለማፍራትና የፈጠራ አድማሱን ለማስፋት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።
የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስማረ መለሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ስምምነቱ የመማር ማስተማር ሂደቱን በኤ.አይ ለመደገፍና የኢንስቲትዩቱን የቴክኖሎጂ
አቅም ለተቋማቸው ዕድገት ለመጠቀም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አወል ሰኢድ (ዶ/ር) በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት ቴክኖሎጂውን በአካዳሚክና በምርምር መስክ ለማስረፅ ስምምነቱ ምቹ
መድረክ እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
የጤናው ዘርፍ ተጠቃሚነትን በተመለከተ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የአካዳሚክ ሜዲካል ዳይሬክተር ለሚ በላይ (ዶ/ር) ሲናገሩ፤ ስምምነቱ የህክምና ስርዓቱን ለማዘመንና ኤ.አይን ለችግር መፍቻነት ለመጠቀም ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ይህ የጋራ ትብብር በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ሲሆን፣ በተለይም በምርምር፣ በሰው ኃይል ልማትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እንደሚያመጣ ይጠበቃል።
Source: Ethiopian Artificial Intelligence Institute