የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የስራ ዉል ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
· MOU
EAII and the Ministry of Planning and Development partner to implement a national digital planning and evaluation system.
ስምምነቱ የተቀናጀ የዲጂታል እቅድ ክትትል እና ግምገማ ሥርዓትን በፌዴራል እና በክልል በሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ ሥርዓቱ በተለይም እንደ ሀገር የሚኖረዉን ኢኮኖሚያዊ ዳታ በአግባቡ ሰብስቦ በመተንተን ጥቅል የሀገር ዉስጥ ምርትን (GDP) ለማስላት የሚያስችል ነው።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ኢንስቲትዩቱ ዳታ ላይ የተመሰረቱ የኤ.አይ ውጤቶችን የማልማት ስራዎችን በሀገር ደርጃ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህ አግባብ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ የሀገሪቱን የእቅድ እና ልማት ስራ በቴክኖሎጂ ለማዘመን ይህንን ሥርዓት በታቀደው ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ በመድረኩ አረጋግጠዋል፡፡
የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ስምምነቱ መንግሥት የሚሰራቸውን ስራዎች በመረጃ ላይ የተመሰረቱ ለማድረግ እና የመረጃዎቹን ትክክለኝነት ለማረጋገጥ መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ጉዞን እውን ለማድረግ ስምምነቱ አቅም እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡
የስምምነት ፊርማውን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) እና የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ተፈራርመዋል፡፡
Source: Ethiopian Artificial Intelligence Institute